ለኢትዮጵያውያን የቀረበ የፍቅር ጥሪ

             የቤት እንሰሳትና የዱር አራዊት ልጆቻችውን ከቀማኛ ገዳይ አውሬ ለመታደግ የተቻላችውን ሁሉ ያደርጋሉ። ሊያጠቃ የመጣውን ገዳይ፣ ከእነሱ የበረታ ቢሆንም እንኳ፣ በቀላሉ እጅ ሳያሰጡ ልጆቻችውን ወደራሳችው በማስጠጋት እነሱ ከለላ ሆነው ልጆቻችውን ከሞት ለመታደግ ይታገላሉ። ከእንሰሳትና ከአውሬ የሚለየን አእምሮ ያለን የሰው ልጆች፣ እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ልጆቻችንን ሊውጥ አሰፍስፎ ከመጣው ከዚህ አውሬ እየጠበቅን እንገኛለን? ወይንስ ከአውሬው ጋር እየተባበርን እንገኛለን? ይህ የማወራላችሁ ጉዳይ አራት እግር ስላለው አውሬ አይደለም። ልጆቻችንን ሊውጥ፣ አገርን ሊደረምስና ሊበታትን የሚያስፈራራውን፣ በሰዎች አእምሮ ውስጥ መሽጎ በወገኖች መካከል የጥላቻን ዘር እየዘራ ስለሚገኘው ክፉ የዘረኝነት መንፈስ ነው።

            ሰው አይቶና ሰምቶ ይማራል፤ ደግሞም ባለእውቀት ይሆናል። ያወቀውን ነገር ትክክል ነው ብሎ ካመነ እምነት አድርጎ ይይዘዋል፣ ያመነበትን ነገር ይኖረዋልና እምነቱ ወደ ተግባር ሲተረጎም ማንነቱንና ባህሪውን ያሳያል። የሰዎች ባህርይና አስተሳሰብ በአብዛኛው በተሰጣቸው ማህበራዊ ትምህርትና ስልጠና ላይ ይወሰናል። ልጆች ወላጆቻችው እንዲያደርጉ የሚነገሯቸውን ያንኑ ያደርጋሉ፤ ከዚህም በላይ ወላጆቻችው ሲያደርጉ ያዩትን ያንኑ ያደርጋሉ። ለነሱ ትልቅ የህይወት ምሳሌ ወላጆቻቸው ናቸው፤ ልጆቻችው ምን አይነት ሰዎች እንደሚሆኑ በመወሰን ረገድ ወላጆች ትልቅ ድርሻ አላቸው። ለእርሻ በተዘጋጀ መሬት ላይ የሚዘራ ስንዴ አዲስ ተክል ሆኖ ለመብቀል የሚያስፈልገውን ሁሉ ካገኘ ጊዜውን ጠብቆ የሚያፈራው ያንኑ ስንዴ ነው። ልጆችም አድገው ለቁም-ነገር ሲደርሱ በልጅነታቸው የተዘራባቸውን ያንኑ እምነትና አስተሳሰብ ከሞላ ጎደል ይዘው ብቅ ይላሉ። ጤነኛ ዘር የተዘራባቸው ጤነኛ አስተሳሰብ ይዘው ህብረተሰቡን ስለሚቀላቀሉ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ፣ ለራሳቸውና ለሌሎች ችግር የማይፈጥሩ ሰላማዊ ዜጎች ይሆናሉ። ወላጆችም በማለዳ የዘሩት መልካም ዘር መልካም ፍሬ አፍርቶ ሲያዩ የረዳቸውን እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።

             ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ ባለፉት ጥቂት ወራት አገራችን ውስጥ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ የተለቀቁ ጽሁፎችንና ቪዲዮዎችን ተመልክቼ መርዛማ የሆኑ አስተሳስቦች በመዘራት ላይ መሆኑ አሳስቦኝ ነው። ለአመታት በምድራችን ላይ ሲዘራ የኖረው የዘረኝነት ዘር ፍሬ አፍርቶ ስራ ላይ መዋል ከጀመረ ቆይቷል፤ ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በዘሩ (በብሄሩ) መለካት ከተጀመረ ሰነባበተ። ዛሬ ግን የዘረኝነት አስተሳሰብ የሚያሳፍር መሆኑ ቀርቶ አለም ሁሉ ይወቀኝ ብሎ ድረ-ገጾችን በማጣበብ ላይ ይገኛል። ይህ ክፉ ዘር ይዞ የመጣ አስተሳሰብ ለሁሉም ኢትዮጵያውያንና ለምንወዳት አገራችን አደጋን የጋረጠ ነው። በተለይም ቀጣዩ ትውልድ ስለራሱና ስለሌሎች ጤነኛ አስተሳስብ ይዞ እንዳያድግ ስለሚያደርግ ማንንም አይጠቅምም፣ አያስተምርም። ህዝብ በዘሩ (በቋንቋው) ልዩነት እንዴት ይሰደባል? በዘራችንና በብሔራችን መመጻደቅና መመካትስ ለምን ያስፈልገናል? እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የትኛውም ዘር ከማንም አያንስም፣ አይበልጥምም። የሰው ልጅ ሁሉ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ እኩል የሚያደርገውን ማንነት ይዞ ተፈጥሯል። በማንነቱ መመካት ካስፈለገው በእግዚአብሄር አምሳል በመፈጠሩ ብቻ ሊመካ ይገባዋል፤ “የሚመካ በእግዚአብሄር ይመካ” ይላል የእግዚአብሄር ቃል።

              በዘሬ የተነሳ ከሌላው የተሻልኩኝ ወይም ያነስኩኝ ነኝ ብሎ ማሰብ  ጤነኛ አስተሳሰብ ከቶ አይደለም። ከየትኛውም አካባቢ ብንፈጠርና የትኛውንም አይነት ቋንቋ ብንናገር ከሌላው የምናንስበት ወይም የምንበልጥበት ምክንያት ሊሆነን አይችልም። ምንም አይነት ተጨማሪ ውበት ማሳመሪያ ሳያስፈልገን ሁላችንም ሙሉ ሰዎች ነን። በሌሎች የሚናቁ የሚመስላቸው ወገኖች ምንም የሚናቅ ነገር እንደሌለባቸው በመገንዘብ ከሚንቋቸው በልጠው ለመታየት መድከም አያስፈልጋቸውም፤ እንዲሁ በቂ ናቸው። ከሌላው የተሻሉ መስለው የሚታያቸውም ቢሆኑ ምንም የሚበልጡበት ነገር ባለመኖሩ እብሪትና መታበይ አያስፈልጋቸውም፤ እነሱም እንዲሁ በቂ ናቸው። እግዚአብሄር የማያዳላ አምላክ ስለሆነ ሁሉንም ወገኖች እኩል መመዘኛ በሆነው በሰው ልጅነት ፈጥሯል፤ የሰው ልጅ በሰውነቱ የተከበረ ነው።

              እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በአሁኑ ጊዜ በአስጸያፊ ደረጃ እየተስፋፋ ማህበራዊ ድረ-ገጾችን እያጣበበ የመጣው የኔ ዘር ከሌላው ይበልጣል የሚለው አስተሳሰብና መርዘኛ ስድቦቹ ካልተለወጠ አእምሮ የሚመነጩ ናቸው። ለራሱ እንዲወደድና እንዲከበር የሚፈልግ ሰው ሌሎችን መውደድና ማክበር ይጠበቅበታል። የራስን ዘር ከሌላው አስበልጦ ያለማየትና ሰዎችን በሰውነታቸው መቀበል ትህትና፣ ያደገ አስተሳሰብም ነው። እግዚአብሔር አእምሯችውን ለመልካም የለወጣቸው ሰዎች ውስጣቸው በእብየትና በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር የተሞላ ስለሚሆኑ ሰውን ሁሉ መውደድ ባህላቸው ይሆናል። የተለወጡ ሰዎች የዘርን ልዩነት ሆነ የቆዳን ቀለም  አያዩም፤ ሰውን ለመውደድ ምንም አይነት ድንበር አይወስናቸውም፤ ሰውን ሁሉ ማፍቀርና ማክበር ነፍሳቸውን ያረካዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን ይህን ክፉ አስተሳሰብ መመከት የምንችልበት ሁነኛ መንገድ በፍቅር ሃይል ራሳችንን መለወጥ ነው።

            ዛሬ በይፋ ወጥተው ማህበራዊ ድረ-ገጾችን በመጠቀም ዘረኛ መርዛቸውን በመርጨት ላይ የሚገኙት ሰዎች አንዳንዶቹ እናቶች ወይም አባቶች ሊሆኑ የሚችሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ታናናሽ ወንድምና እህት ያላቸው ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከሚያስተላልፉት የስድብና የጥላቻ ቃላት፣ አንዱን ወይም ሌላውን ዘር ከሚያንቋሽሽ ቪዲዮ፣ መጣጥፍ፣ ምስልና ንግግር አዲሱን ትውልድ የሚያስተምር ምን ነገር ይገኛል? ብሄራችን ወይም ዘራችን ለምንለውስ ምን ፋይዳ ያተርፋል? እንዲያውም ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልን፣ ከመቻቻልና ከይቅርታ ይልቅ በቀልን የሚያስፋፋ እንጂ። ይህ መርዝ ቀጣዩን ትውልድና የወደፊቷን ኢትዮጵያ ጥቅም የሚያጨናግፍ በመሆኑ እነዚህ ወገኖች በአእምሯቸው የነገሰውን አስተሳሰብ በጽሞና እንዲመረምሩ እለምናቸዋለሁ። እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ መርዝ ራሳችንን ጠብቀን በምድራችን ሰላም፣ መከባበርና መፈቃቀር ይሰፍን ዘንድ የየድርሻችንን እየተወጣን ከጥፋት ይልቅ የመፍትሄ አካሎች መሆን ይገባናል። የሰው ልጅ የህይወት አላማ በፍቅር መኖርና ፍቅርን መዝራት ነው። ፍቅር ግለሰብን፣ ህዝብንና አገርን ይፈውሳል። እግዚአብሔር ፍቅር ነውና የሰላም አለቃ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ልባችንን ወደ ይቅርታና ወደ ፍቅር ይመልስልን።

             ሩዋንዳ ዘርን መነሻ ባደረገ ግጭት ምክንያት በአለም ታሪክ ውስጥ በአሳዛኝነቱ ሲታወስ የሚኖር የህዝብ ፍጅት የተፈጸመባትና ቢያንስ አንድ ሚሊዮን (በቅርብ መውጣት የጀመሩ መረጃዎች እስከ ሁለት ሚሊዮን ያደርሱታል) ህዝብ ያለቀባት አገር መሆኗ ይታወቃል። ከአራት አመት በፊት ሩዋንዳን የመጎብኝት እድል አግኝቼ ስለነበር የመከራውና የሀዘኑ ጥልቅት የአገሪቱን ዜጎች ምን ያሀል እንደጎዳ ለማየት በቅቻልሁ። በሩዋንዳ ቆይታዬ የዘር ጭፍጨፋውን ቤተ-መዘክር ተመልክቻለሁ፤ አሳዛኝ የጭፍጨፋ ፎቶ ግራፎችን፣ እጅግ በዙ የሰው አጽሞችን፣ እንዲሁም ታሪኩን የሚያሳዩ ቪድዮ ..ወዘተ ተመለከትሁ። ያየሁትና የሰማሁት ነገር ሁሉ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ አሳመመኝ፤ ሙዚየሙ ውስጥ ገብቼ እስክወጣ ድረስ እንባዬ ከቁጥጥሬ ውጭ ያለማቋረጥ ይፈስ ነበር። በእልቂቱ ምክንያት ቤተ ሰቦቻቸው ያለቁባቸውን በርካታ ቤተ-ሰቦች አግኝቼም አነጋግሬ ነበር። ባሏንና ስድስት ልጆቿን በአንድ ጊዜ ያጣች እናት የሆነውን ሁሉ አውጥታ ባጫወተችኝ ጊዜ የእናትነት ልቤ ቢሰበርም ይህን ሃዘን ተሸክማ በህይወት እንድትኖር ያስቻላት የእግዚአብሔር ጸጋ ግን አስደነቀኝ፤ በሩዋንዳ የተፈጸመው የዘር ፍጅት የሰው ልጅ በታሪኩ የፈጸመው ትልቅ ጥፋት ነው። ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሩዋንዳ ታሪክ ጠንቅቀን ልንማር ይገባናል ብዬ አምናለሁ። እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ ጥፋት በእኛም ሆነ በማንም አገር ላይ ሊደገም አይገባም። ዛሬ ሩዋንዳውያን እኔ ቱሲ ነኝ፣ እኔ ሁቱ ነኝ አይሉም፤ ሁሉም ሰው ሩዋንዳዊ ነኝ ባይ ሆኗል፤ በመካከላቸው ዳግም ይህ ታሪክ እንዳይደገም ተስማምተዋል፤ ከመራራው ታሪካቸው ተምረው የአንድነት መንፈስ ረብቦባቸዋል፤ ኤኮኖሚያቸው በጥሩ ሁኔታ በማደግ ላይ ነው። ለዚህ የበቁት ከፈጸሙት ስህተት ተምረው ልባችውን ለይቅርታና ለአንድነት ስላዘጋጁ ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍልዋል። እኛ ከእነሱ ብንማር በተመሳሳይ ክፍያ ማለፍ አይኖርብንም። ሩዋንዳን የጎዳውን አደገኛ የዘረኝነት ጎርፍ እኛም ዘንድ ሳይደርስ ተባብርን ልናሰቆመው እንችላለን።

            ዛሬ በአገራችን ስር ስዶ የምናየውን የዘር ክፍፍል ከወዲሁ ለመመከት ይቻለን ዘንድ የትኛውንም አይነት ዘር እንወክላለን የምትሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አገር ወዳድ ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በስሜት ከመገፋት ወጥተን የነገሮችን አደገኝነት በጥሞና ማየት የሚገባን ጊዜ ላይ ነን፤ በእርቅና በይቅርታ መንፈስና ድርጊት አንድ መሆን የሚገባን አጣዳፊ ወቅት አሁን ነው፤ በቅንነት ልብ፣ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለፍትህ የተቀደሰ አላማ እስከቆምን ድረስ አምላካችንም እርዳታው ከኛ ጋር ይሆናል።

            ይህች ልባዊ ማስታውሻ በአለም ዙሪያ በዘር ግጭት የተነሳ ልጆቻቸውን ላጡ እናቶች ትሁንልኝ።

           ሙሉ ግርማይ ላይኔ

  1. Suzanne ChrismanSep 15, 2016

    Tamrat,

    I rejoice in hearing this good report concerning your Sudan trip. Let us know if you have an English version of the latest update, 9-14.
    Prayers,
    Suzanne

Leave a Reply